የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ በሰላምና ደህንነት መስኮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ በሰላምና ደህንነት መስኮች እንዲሁም ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ የነበራቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሞሳድ ቢሮ ኃላፊ ጋር በዛሬው ዕለት ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል ።
በውይይታቸውም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሞሳድ ጋር ትብብሩን በማጠናከር በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታ ሥልጠና ዘርፍ ይበልጥ ተባብረው ለመሥራት ማቀዳቸው ተገልጿል ።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በውይይቱ ወቅት ÷ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሞሳድ የሚደረግለትን ሁሉን አቀፍ የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፎች በመጠቀም ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከልና ከሥሩ በመንቀል ረገድ ያላት አቋም ጠንካራ መሆኑን የጠቀሱት በእስራኤል የሞሳድ ዳይሬክተር ጀነራል ሚስተር ዮሴፍ ኮ`ን ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሞሳድ ቢሮ ኃላፊ የህዝቦች የጋራ ጠላት የሆነውን ሽብርተኝነትን በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል ሙሳድ ከኢትዮጵያ አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋም ጋር በትብብር እንደሚሰራና ድጋፋኑም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሞሳድ ኃላፊው በእስራኤል የሞሳድ ዳይሬክተር ጀነራል ሚስተር ዮሴፍ ኮ`ን ስም ለተቋሙ የተላከውን የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁሶች የፊት ጭምብል፣ ቬንቲሌሽን፣ለህክምና ባለሙያዎች የሚያገልግሉ አልባሳቶችን ድጋፍ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስረክበዋል።
ኢትዮጵያና እስራኤል በባህል፣ በሃይማኖት፣ በታሪክና በፖለቲካው ዘርፎች የረጅም ጊዜ ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመረጃና ደህንነት ዘርፉ ያላቸውን ተቋማዊ ግንኙነት እያጠናከሩ መምጣታቸውን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል ።