በጋምቤላ ክልል በህወኃት ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ መክሸፉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በጋምቤላ ክልል በህወሃት ጁንታ ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ጁንታው በክልሉ ዘርግቶት የነበረውን የጥፋት መረብ ሙሉ ለሙሉ ለመበጣጠስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት፤ በጁንታው ታቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ መረጃ ቀድሞ በመድረሱ በጸጥታ ኃይል አስፈላጊው ጥናት ተካሄዶ ሴራውን ማክሸፍ ተችሏል።
አቶ ኡሞድ “በዚህም ችግር ሊፈጥሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ነው ያሉት።
የህወሃት ጁንታ ሴል በክልሉ በብዛት እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ኡሞድ፤ “ክልሉ የቡድኑ የጥቃት ኢላማ ይሆናል የሚል ስጋት በመኖሩ ሰፊ የመከላከል ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።
አካባቢውን የብጥብጥ ቀጠና እንዲሆን አቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ በህዝብና በጸጥታው ሃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን አስታውቀዋል።
የቡድኑን ሴሎች በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ የቀሩ መኖራቸውን ጠቁመው ቀሪዎቹን ለመያዝም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኙ ስምንት የመውጫና መግቢያ በሮች መኖራቸውን አስታውሰው፤ የጥፋት ቡድኑ አባላት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመኮብለል እየሞከሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ድንበር አቋርጠው ለመውጣት የሞከሩ የቡድኑ አባላት መያዛቸውን ጠቁመው፤ “የጥፋት ቡድኑን መንገድ በመምራት ለማሸሽ የሞከሩ ሶስት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአካባቢ አስፈላጊው የጸጥታ ኃይል ተመድቦ የተጠናከር ክትትልና ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የጁንታው ሴራ እስከ መጨረሻው ለማምከን በተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ ከህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 65 ግለሰቦች የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ መዘገቡ ይታወሳል።