በዓለም ላይ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሚሊየን አለፈ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 60 ሚሊየን ማለፉ ተገለጸ።
እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ እስካሁን በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች 60 ሚሊየን 420 ሺህ 355 ደርሷል።
ከእነዚህ መካከል 38 ሚሊየን 704 ሺህ 716 የሚሆኑት ደግሞ ከወረርሽኙ ማገገማቸው ተሰምቷል።
ወረርሽኑ ከተከሰተበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመላው ዓለም የ1 ሚሊየን 421 ሺህ 650 ሰዎችን ህይወት አልፏል።
ወረርሽኙ እየተስፋፋባቸው ከሚገኙ ሀገራት መካከል አሜሪካ ዋነኛ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።
አስካሁን ድረስ በአሜሪካ ከ12 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ በህንድ ከ9 ሚሊየን በላይ፣ በብራዚል ከ6 ሚሊየን በላይ፣ በፈረንሳይና በሩሲያ ከ2 ሚሊየን በላይ፣ በስፔን እና በእንግሊዝ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ፣ በጣልያን፣ በአርጀንቲና፣ በኮሎምቢያ እና በሜክሲኮ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
እስካሁን ከፍተኛ ሞት ከተመዘገበባቸው ሃገራት መካከል አሜሪካ 262 ሺህ 266፣ በብራዚል 170 ሺህ 769፣ በህንድ 135 ሺህ 223 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በአፍሪካ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ 775 ሺህ 502 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 716 ሺህ 444 ሰዎች ማገገማቸውን ነው የተሰማው።
ይህም በደቡብ አፍሪካ በወረርሽኙ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው መረጃዎቹ የሚያሳዩት።