Fana: At a Speed of Life!

የቱርክ ፍላጎት በኢትዮጵያ የማይናጋ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት እና ያልተሸራረፈ የግዛት ሉዓላዊነት እንዲኖር ነው-ያፕራክ አልፕ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማት እና ሉዓላዊነት እንደምትሻ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር እና በአፍሪካ ሕብረት የቱርክ ቋሚ ልዑክ ያፕራክ አልፕ ገለፁ፡፡

በአምባሳደሯ የተመራው ልዑካን ቡድን፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ጉዳዮች እና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ በተወያዩበት ወቅት ነው ይህን የገለፁ፡፡

አምባሳደሯ በዚህን ወቅት ከ1888 ዓ.ም.ጀምሮ እስካሁን ተጠናክሮ የቀጠለው የሁለቱ ሉዓላዊ ሀገራት ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ተምሳሌታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቱርክ ፍላጎት በኢትዮጵያ የማይናጋ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት እና የአልተሸራረፈ የግዛት ሉዓላዊነት እንዲኖር መሆኑን አምባሳደሯ ገልፀዋል፡፡

ቱርክ እንደ ሀገር ወደ አፍሪካ አህጉር ለምታስባቸውም ሆነ ለምታካሂዳቸው ማናቸውም ጉዳዮች ኢትዮጵያ ቀዳሚ መዳረሻ ሆና መቆየቷን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የቱርክ አየር መንገድ አዲስ አበባን ላለፉት በርካታ ዓመታት ቀዳሚ መዳረሻው አድርጎ መሰንበቱን እና በኢንቨስትመንቱ ረገድ ያለውን የላቀ ትስስር በአስረጂነት ጠቅሰዋል፡፡

ቱርክ ከእነዚህም ባሻገር በትምህርት ዘርፍ የተፈጠረው መተባበር እንዲጎለብት እና በባሕል ዘርፍም ቢሆን በኢትዮጵያ የቱርክ የባሕል ማዕከል በመገንባት ጭምር ትስስሩ እንዲያድግ እንደምትሻ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ጠቁመዋል፡፡

ቱርክ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 200 ኩባንያዎች እንዳሏት የገለፁት አምባሳደሯ እነዚህም አማካይነት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ ኢትዮጵያ ውስጥ አፍስሰዋል ነው ያሉት፡፡

25 ሺህ ኢትዮጵያውንም በእነዚህ ኩባንያዎች ተቀጥረው ራሳቸውን ከማስተዳደራቸው በላይ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርም እያካሄዱ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት በኤምባሲ ደረጃ ግንኙነት ከጀመሩበት ከ1954 ዓ.ም. ወዲህ ወዳጅነታቸው አብነታዊ በሆነ መልኩ ማደጉ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በትምህርት ዘርፍ ቱርክ በየዓመቱ ከ100 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የምትሰጠው ዕድል፤ የኢትዮጵያን የወደፊት መሪዎች እና የልማት ግንባር-ቀደም ተዋኒያንን ከመፍጠር አኳያ የሚደነቅ ነውም ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰባሳቢ አያይዘውም፤ ምንም እንኳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ እንደሰጡ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከፓርላማ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በሉዓላዊ የግዛት ወሰኗ ሕግን የማስከበር እና የሉዓላዊነት ዘመቻ እንጂ፤ አንዳንድ የተሳሳቱ መገናኛ ብዙሃን እና ግለሰብዎች እንደሚሉት ከፓርቲ ወይም ከሆነ ብሔረሰብ ጋር የሚካሄድ የጦርነት ግጭት አለመሆኑን ለቱርክ ልዑካን አስረድተዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.