የትምህርት ሚኒስቴርና የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና አመራሮችና ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ለገሱ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የትምህርት ሚኒስቴር እና የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አመራሮች እና ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አመራሮች እና ሰራተኞች “ደሜን ለህግ መከበር ህይወታቸውን ለሰጡት ለመከላከያ ሰራዊት አባላት” በሚል መሪ ቃል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ እና የ3 ሚሊየን ብር ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
በደም ልገሳ መርሃ ግበሩ ተገኝተው የተገኙት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ አድማሱ አንጎ፥ ለሀገር መከላከያ ስራዊት ደም መለገስ ብቻ ሳይሆን የተቋሙ አመራሮች፣ ሰራተኞች እና ተቋሙ 3 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በሀገር መከላከያ ስራዊት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሕግ የማስከበር እና ሁሉም ሰው ከሕግ በታች መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ አድማሱ አክለውም፥ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የሕግ የበላይነት የሚያረጋግጥ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገባት የሚያስችል በመሆኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ሁሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ያለና በቀጣይም ይህንን ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞችም “ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ” በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት የደም ልገሳ አካሂደዋል።
በደም ልገሳ ፕሮግራሙም ከሚኒስትሩ አመራሮች እና ሰራተኞች በተጨማሪ የክልል እና ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ አመራሮች እና ተወካዮችም ተሳትፈዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በዚሁ ጊዜ፥ የደም ልገሳው መርሃ ግብሩ ዓላማ የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ ላይ ለተሰማራው የመከላከያ አለኝታን ለማሳየት ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስም የትምህርት ሚኒስቴር ለመከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።