የጥፋት ቡድኑ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገ ነው – ፖሊስ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህወሓት የጥፋት ቡድን በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ጦርነቱን አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሳለን ብሎ ሃገር የመናድ ጦርነት የለኮሰው የህወሓት ጁንታ አሁን ላይ ሽንፈት እየተከናነበ መሆኑን ገልጿል።
ጽንፈኛው ቡድን በከፈተው ጥቃት በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ22 በላይ የልማት አውታሮችን ለአመታት በጠበቁ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ አባላት መኖሪያ ካምፖች ላይ ጥቃት በማድረስ በርካታ አባላት ላይ የግድያና የአፈና ወንጀል መፈፀሙን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የህወሃት ጁንታ በመፈፀመው ክህደት መንግስት እየወሰደው ባለው ህግ የማስከበር እርምጃ እየተዳከመ በመሆኑ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ይገኛለ።
በዚህም የጁንታው ቡድን አባላትና ተላላኪዎች በግዙፍ ፕሮጀከቶች ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልፇል።
በመሆኑም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎችና ሰብስቴሽኖች፣ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ጥበቃው መጠናከሩን ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።
በቦሌና በየክልሉ በሚገኙ ኤርፖርቶች፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በውሃ ግድቦች፣ በነዳጅ ዲፖዎች፣ ፋብሪካዎችና ድልድዮችም እንዲሁ።
በስደተኛ ካምፖች፣ በሳተላይት ጣቢያዎች እና በማዕድን ማውጫዎች ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉትን ጥቃቶች አስቀድሞ ለማክሸፍ ጥብቅ ክትትልና ቋሚ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በቤተ መንግስትና በክልል ምክር ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶች፣ በባንኮች፣ በምድር ባቡር ፕሮጀክቶች፣ በቢሮዎችና መኖሪያ ካምፖች፣ በዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች፣ ንዲሁም ሌሎች የልማት አውታሮችና የጠረፍ ከተሞችም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ይላል የኮሚሽኑ መግለጫ።
በግዳጅ ላይ የነበሩት የፌዴራል ፖሊስ አባላት የጁንታውን ጥቃት በመከላከል በአንዳንድ ግንባሮች ከጀግናው አገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን በግንባር እየተፋለሙም ይግኛሉ ብሏል።
በሰሜንና በምዕራብ ቀጣና፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና መተከል ዞን እና አካባቢው፣ በደቡብ ቀጠና በሚዛን ቴፒ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወላይታ ሶዶ እና ኮንሶ አካባቢዎች የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሯልም ነው ያለው።
በተጨማሪም ከነገሌ ቦረና እስከ ሞያሌ፣ በምስራቅ ቀጠና ከአዋሽ እስከ ጋላፊ እንዲሁም በሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች ጥብቅ ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።
ከክልሎች የፀጥታ ሃይልና በየቦታው ካለው የመከላከያ ሰራዊት ጋር ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅም እንዲሁ።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ከጁንታው እኩይ አላማ ጋር ተያይዞ በወንጀል የጠረጠራቸውን 93 የህወሃት ጁንታና የኦነግ ሸኔ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ጠቁሟል።
በተደረገ ፍተሻና አሰሳ እንዲሁም በህብረተሰቡ ጥቆማም 30 የመከላከያና የፖሊስ የደንብ ልብስ፣ 47 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 43 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 1 ሺ 376 የተለያዩ ጥይቶች ፣ 7 ቦምቦች፣ 2 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 102 ድምፅ አልባ መሳሪያዎች ተይዘዋል።
በተጨማሪም 8 የእጅ ራዲዮ መገናኛ፣ የተለያዩ የቴሌኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎች፣ 534 ሺ 870 ብር እና የተለያዩ ተሸከርካሪዎች መያዛቸውንም ገልጿል።
ይህም በዜጎች እና የፀጥታ አካላት ትብብር የተገኘ ውጤት መሆኑን ያመለከተው መግለጫው የህዝቡ ትብብር አሁንም እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።