በውጊያ ስለማላምን 150 ጥይት ተስጥቶኝ አንድም ጥይት ሳልተኩስ ነው እጄን የሰጠሁት- ወጣት አብረኸት
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የ21 አመት ወጣት ናት የሆነችው የአብረኸት የጁንታው ታጣቂ የነበረችና እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ከሰጡ ውስጥ አንዷ ነች።
ወጣቷ በ2011 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ስልጠና ወስዳለች፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ሁና ነገሌ ቦረና ተመድባም ግዳጇን እየተወጣች ሳለ በጠና ታማ ከውትድርናው ዓለም ተሰናብታ ወደ ቤተሰቦቿ መመለሷን ትናገራለች።
የአብረኸት ህመም መጥናት ከምትወደው መከላከያ ቢለያትም ከጁንታው ዕይታ ግን መሰወር አልቻለችም።
በጠላ ንግድ የሚተዳደሩትን እናቷን እያገዘች ኑሮን ብትቀጥልም፤ የጁንታው አባላት የአብረኸትን ወታደርነት ያውቁ ነበርና የጁንታውን ታጣቂ እንድትቀላቀል በእናቷ በኩል ግፊት ማድረግ ጀመሩ።
ጁንታው የአብረኸትን እናት ሌት ተቀን በማስፈራራታቸው ልጃቸውን ሳይወዱ በግድ ለታጣቂው አስረከቡ፤ አብረኸትም ቤተሰቦቼን ለአደጋ ከማጋልጥ በሚል ታጣቂውን ተቀላቀለች።
“ሌላ ስራ በቀላሉ ማግኘት ስላልቻልኩና ጫናውና ማስፈራሪያው ሲበዛብኝ ታጣቂውን ተቀላቀልኩ፤ የቤተሰቡ አባላት ሰባት ነን ፤ አባቴ በህይወት የለም፡፡ እናቴ ብቻዋን ነው ጠላ ሽጣ ያሳደገችኝ ስትል ገልፃለች፡፡
እሷን ለማገዝ ስልም ነው ወደዚህ የገባሁት” ስትልም ነው የታጣቂው አባል የሆነችበትን አጋጣሚ የምታስታውሰው።
አብረኸት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ እየወሰዱት ባለው ህግ የማስከበር እርምጃ ላይ እጇን የሰጠችው አንድም ጥይት ሳትተኩስ መሆኑን ትናገራለች፤ “150 ጥይት ተስጥቶኝ አንድም ጥይት ሳልተኩስ ነው እጄን የሰጠሁኝ።
ምክንያቱም በዚህ ውጊያ አላምንበትም፤ እየሞተ ያለውም የደሀው ልጅ ነው፤ እጄን ከሰጠሁ በኋላም ቢሆን ሶስት ቀን ሙሉ የሰራዊቱ አባላት ከሚበሉትና ከሚጠጡት እያካፈሉኝ ቆይቻለሁ ነው ያለችው።
በትግራይ ክልል በየአካባቢው ያለው ወጣት ተገዶ ወደ ግዳጅ እንዲገባ ተደርጓል የምትለው ወጣቷ፤ ስልጠና የሚሰጠውም የይድረስ ይድረስ መሆኑን አልሸሸገችም፤ “ለአጭር ጊዜ ክላሽ እንዴት እንደሚፈታና እንደሚገጠም፣ ኢላማ እንዴት እንደሚመታ አሳይተው ብቻ ነው ወደ ጦርነት የሚማግዷቸው ብላለች፡፡
ይህ ደግሞ የህወሓት አመራሮች ለትግራይ እናቶችም ሆነ ወጣቶች ደንታ እንደሌላቸውና የራሳቸውን የስልጣን ጥም ለማርካት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ያሳያል” ነው ያለችው፤ አብረኸት፡፡
“የህወሓት አመራሮች፤ የትግራይን ህዝብ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚጠላው፣ የትም ሄደው በሰላም መኖር እንደማይችሉ አድርገው ወጣቱንንም ሆነ ህጻናትን ጭምር ይሰብካሉ፤ ህዝቡም ህወሓትን ስለሚፈራ የሚሉትን ለማድረግ ይገደዳል ያለችው ወጣቷ ይህ ሰላም የማይወድ ድርጅት ውጤት ለማያመጣ ነገር ወጣቱን እያስፈጀ ነው” ብላላች።
የህወሓት ጁንታ ወጣቱን መስዋዕት የሚያስከፍሉት የማይሆን ነገር እየሞሉት፣ እያስገደዱትና፣ በገንዘብም እያታለለሉት ጭምር መሆኑን አብረኸት ትናገራለች።
የትግራይ ህዝብ መከላከያን እንዲወጋ አይፈልግም፤ ምክንያቱም መከላከያ የትግራይ ህዝብን ደህንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ትምህርት ቤት እየሰራ፣ ጤና ጣቢያ እየገነባ የኖረ ወገን ነው፤ የምትለው አብረኸት፤ “ወርቅ ለአበደረ ጠጠር እንዲሉ እኛን አታለው እንደ ቤተሰብ የምናየውን መከላከያ ሰራዊትን እንድንወጋ አድርገውናል” ስትል ከኢፕድ ጋር በነበራት ቆይታ በከፍተኛ ጸጸት ውስጥ ሆና ተናግራለች።
“የህወሓት ቡድን እንደሚለው መከላከያ እኛን ቢጠላን ኖሮ እንዴት ትግራይን ይጠብቃታል” ስትልም ትጠይቃለች።
“እኛ ምንግዜም ኢትዮጵያዊ ነን፤ አጸያፊ ስራ እስካልሰራን ድረስ ህዝቡ ዝም ብሎ አይጠላንም፤ በመሆኑም የትግራይ ወጣቶች ዓላማ የሌለው ጦርነት ውስጥ መግባት የለባቸውም።
ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን በመስጠት በሰላም መኖር ይኖርባቸዋል” ስትል ሀሳቧን ገልፃለች።