መንግስት በወህሓት አጥፊ ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በህወሓት አጥፊ ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልፀዋል።
በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ክልላዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ምክክር አድርገዋል።
በሀዋሳ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይም የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ፣ የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ፣ የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሞቻ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የዶንጋ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ተሳትፈዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይቱን ተከትሎ በጋራ ባወጡት መግለጫም፥ “በትግራይ ክልል የአካባቢን ሰላም በመጠበቅና በልማት ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የህዝብ ደጀን በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የህወሓት ቡድን ጥቃት መክፈቱና ዝርፊያ ለማካሄድ መንቀሳቀሱ የሀገር ክህደት ተግባር በመሆኑ ድርጊቱን እናወግዛለን” ብለዋል።
የሀገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ እንዳሁም የህውሓት ቡድን ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰራውን የሴራ ፖለቲካ ለማምከን መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉም አስታውቀዋል።
የትግራይ ህዝባችንና የፀጥታ አካላት በጥፋት ላይ ከተሰማራው ጥቂት የህውሃት ስብስብ ራሱን በማራቅ ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት ከመከላከያ ሀይል ጐን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የክልሉ እና የመላው ሀገሪቱ ህዝቦችም በየትኛውም አካባቢ ለሰላምና ፀጥታ ስራ አስጊ የሆኑ ነገሮችን ነቅቶ በመጠበቅ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባባር ሰላማቸውን እንዲያስጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።
የህወሓት ህገወጥ ቡድን ላይ በሚወሰድው የሀገር ሰላምና ደህንነት የመታደግ ዘመቻ ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚያደርጉም አስታውቅዋል።
የክልሉ እና የመላው ሀገሪቱ ህዝቦችም የሚጠቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።