የከተሜነት ዕድገትን የሚመጥኑ ስራዎች መጠናከር አለባቸው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያዘጋጀው የክልላዊ ልማት ፕላን መድረክ ተካሄደ፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የከተሜነት ዕድገትን የሚመጥኑ ስራዎች በፍጥነት ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር “ክልላዊ ስፓሻል ልማት ፕላን ለተመጣጣኝ ሀገራዊ እድገት እና ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ሃገር-አቀፍ
መድረክ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል።
አቶ ደመቀ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሃገሪቱ የከተሜነት ሂደት ረጅም ዘመን ከማስቆጠሩ አንፃር ዕድገቱን የሚመጥኑ ስራዎች በፍጥነት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የክልላዊ ስፓሻል የልማት ፕላን ዝግጅት እና የከተማ ሙከራ ማዕከል ምስረታ ከሃገራዊ ለውጥ ጉዞ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከህዝብ ብዛት ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ ከተሞች ሊሸከሙ የሚችሉበትን ኢኮኖሚያዊ አቅም አስቀድመው በመገንባት ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በቀጣይ ተግባራዊ በሚደረገው ዕቅድ መሰረት በተለያየ ደረጃ በከተሞች እና አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥነት እና የከተሞች ዘፈቀዳዊ
መስፋፋት በዘላቂነት ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በተጨማሪ የክልላዊ ስፓሻል ልማት እና ክላሰተር ፕላን ማዘጋጀትና የከተማ መሬት አሰተዳደር ስርዓቱን ማዘመን በዕቅዱ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ገልፀዋል።
የከተሜነት እድገት ስርዓት ተመጋጋቢ፣ የተመጣጠነ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በውጤታማነት ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በትኩረት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልላዊ ስፓሻል የልማት ፕላን ዝግጅት እና የከተማ ላብራቶሪ ምስረታ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።