ፌስቡክ አንድሮይድን የሚተካ የራሱን ኦፕሬቲንግ ሲስተም እያበለፀገ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፌስቡክ የራሱን ኦፕሬቲንግ ሲስተም እያበለፀገ መሆኑን ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።
ኩባንያው የራሱን ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚሰራውም ከጎግል አንድርይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም እና ከአይፎን አይ.ኦ.ኤስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ አንደሆነም ታውቋል።
አዲሱ የፌስቡክ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ሙሉ በሙሉ ከዜሮ ተነስቶ በራሱ መንገድ እየበለፀገ መሆኑንም ኩባንያው አስታውቋል።
ኦፕሬቲንግ ሲስተሙ በምን መልኩ ይሰራል የሚለው ነገር በግልፅ ባይታወቀም የፌስቡክ የቪዲዮ የስልክ ጥሪን ጨምሮ ሌሎች የኩባንያው አገልግሎቶች ግን ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው።
ፌስቡክ አሁን በሚያመርታቸው መገልገያዎች ላይ በብዛት የጎግል አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተመን የሚጠቀም ሲሆን፥ ይህም ጎግል በአብዛኛው የፌስቡክ አገልግሎቶች ላይ በበላይነት እንዲቆጣጠር እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ፌስቡክ የራሱን ኦፕሬቲንግ ሲስተም መስራቱም ከጎግል አንድሮይድ ጥገኝነት የሚያላቅቀው መሆኑን እና በሚያመርታቸው መገልገያዎችን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ስልጣን እንዲኖረው እንደሚያደርገውም ተገልጿል።
ምንጭ፦ www.techworm.net