የቻይናዋ ቺንግዳኦ ከተማ ለዘጠኝ ሚሊየን ነዋሪዎቿ በአምስት ቀናት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ልታደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይናዋ ቺንግዳኦ ከተማ ለዘጠኝ ሚሊየን ነዋሪዎቿ በአምስት ቀናት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ በዘመቻ ምርመራ ልታካሂድ መሆኑን አስታወቀች፡፡
የዘመቻ ምርመራው ከውጭ ሃገራት የተመለሱ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትትል የሚያደርጉበት ሆስፒታል ውስጥ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ከተገኙ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
በሆስፒታሉ ውስጥ ስድስት ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የጤና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ጉዳይ የተሰማው ቻይና ከአንድ ሳምንት በፊት ወርቃማው ሳምንት የሚል ክብረበዓል ካካሄደች በኋላ ነው ተብሏል፡፡
የከተማዋ ባህልና ቱሪዝምም ከተማዋ በዚህ ወቅት ከ4 ሚሊየን በላይ ጎብኚዎች እንደምታስተናግድ ነው የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ የጤና ባለሙያዎችንና በሆስፒታል ክትትል የሚደረግላቸውን ሰዎች ጨምሮ እስካሁን ከ114 ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የኮሮና ቫይረስ መነሻ የሆነችው ሁዋን ከተማ በዘመቻ 11 ሚሊየን የከተማዋን ነዋሪዎች መመርመሯ ይታወሳል፡፡
በቻይና በአሁኑ ወቅት 58 ሺህ 578 ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን 4 ሺህ 634 ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ