ህዝብን ማእከል ያደረገ የሰላም ግንባታ ስራ ወሳኙ ተግባር ነው-የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ ከብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን አወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ወይዘሮ ሙፈሪያት እርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ተቋማዊ ነፃነቱ የተጠበቀና በየትኛውም ጉዳይ በስራቸው ጣልቃ የማንገባ ቢሆንም በጋራና በትብብር የምንሰራቸው ጉዳዮች በመኖራቸው የሚና መደበላለቅ ሳይኖር ተቀራርቦና ተጋግዞ መስራት ስለሚያስፈልግ የተዘጋጀ ውይይት ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ግንባታ ስራው ህዝብ ተኮር መሆን አለበት ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ልሂቃን ላይ ያልተንጠለጠለ ፖለቲካ መገንባት ያስፈልገናልም ብለዋል፡፡
በቀጣይም የሰላም ሚኒስቴር እና ብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰፊ የህዝብ፣ የልሂቃን እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የውይይት መድረኮችን በመክፈት የሰላም እና የእርቅ ስራ በትብብር የሚሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ አመት ወደ ህዝብ በመግባት ወደ መሬት የወረዱ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ እኛ የምንሰራው ዘላቂ ትውልድ ተሸጋሪ ሰላም ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
የኮሚሽኑ አባላትም የሰላም ሚኒስቴር በሃገሪቱ ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ፤ ተቋሙን እንደ ዋነኛ አጋር የምንመለከተው ነው ማለታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡