የመዲናዋ አስተዳደር ካቢኔ በጤና ተቋማት ለሚሰሩ ሰራተኞች የገቢ ግብር ወጪን ለመሸፈን ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በጤና ተቋማት ለሚሰሩ ሰራተኞች የገቢ ግብር ወጪን ለመሸፈንና እና በ669 ሚሊየን ብር በፊንፊኔ ልዩ ዞን ለሚገኙ ተማሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ውሳኔ አሳለፈ።
በዚህም የወቅቱ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራቱ እና በከተማዋ ከተከሰተበት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የህክምና አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በማስተባበር የተሠማሩ በከተማው አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የጤና ተቋማት ሁሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ይህ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስጋት መሆኑ እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ የገቢ ግብር ወጪያቸውን ለመሸፈን ውሳኔ አሳልፏል።
በተመሳሳይ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ለእድገት እና ልማቷ ብዙ ግብዓቶችን እያገኘች እድገት እና መስፋፋቷም ሲፋጠን በዙሪያዋ ላሉ ነዋሪዎች ትሩፋት እንጂ መከራና መሰደድ መሆን የሌበትም ያለው ካቢኔው፡
በከተማዋ የተጀመረውን የትምህርት ተሞክሮ እና አገልግሎቶች በአካታች ልማት መርህ መሰረት በፊንፊኔ ልዩ ዞን በሚገኙ 346 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ 152 ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም 669 ሚሊየን 210 ሺህ 780 ብር የትምህርት ቁሳቁስ፣ የተማሪ ደንብ ልብስ፣ ጫማ እና የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እንዲቀርብ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ውሳኔ አሳልፏል።