አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በ24 ሰዎች ላይ ክስ ተከፈተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ጃዋር መሃመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በ24 ሰዎች ላይ ክስ ተከፍቷል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አድናን፣ እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN)፤ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል የፌደራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶች አስከፍቷል፡፡
ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡