የኮሮና ቫይረስ ህክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ 380 የመተንፈሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ፣ የአሜሪካን እና የእንግሊዝ መንግስት እና ኤፍ.ሲ.ዲ.ኦ የተባለ ልማታዊ ድርጅት በጋራ በመሆን የኮሮና ቫይረስ ህክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ 380 የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢነትን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስት የኮቪድ ህክምና ለመስጥት አስፈላጊ የሆነውን የመተንፈሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጋቸው ብዙዎችን ከሞት እንድንታደግ ይረዳል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ ሚካኤል ሰርቫዲዬ በበኩላቸው የመተንፈሻ መሳሪያዎቹ በፅኑ ህሙማን ክፍል ለሚገኙ ታካሚዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በድጋፍ ከተገኙት 380 የመተንፈሻ መሳሪያዎች መካከል 100 የሚሆኑት በቅርቡ ለተመረቀው የአዲስ አበባ ኮቪድ 19 ፊልድ ሆስፒታል የሚሰጡ መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡