ከዘመን ወደ ዘመን የምናደርገው ሽግግር ትርጉም እንዲኖረው አዲስና ተራማጅ አስተሳሰብን ልንላበስ ይግባል – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ ዓመት ዋዜማ በዓል ዛሬ በተመረቀው ሸገር ፓርክ የወዳኝነት አደባባይ በድምቀት ሲከበር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ለመቀበል የዋዜማ ምሽት ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከፊታችን ምንም ያልተፃፈበት የዘመን መፅሃፍ ተዘርግቷልና እንኳን አደረሰን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
የሰው ልጅ ባለፈው ነገር ተቸክሎ እንዳይቀር እንደገና በአዲስ ተስፋ፣ ጉልበትና ሀሳብ እንዲነሳ አዲስ ዓመት አንዱ መድሃኒት መሆኑ አንስተዋል።
የአዲስ ዓመት ዋዜማ ያለፈውን ወደኋላ ወስደን እንድንገመግመው፣ እንድናበጥረውና እንድናበረየው ያደርጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ፥ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ወደፊት እንድንተልም የሚያደርግም ነው ብለዋል፤ ምንም ያልተነካ አንድ ዓመት ሙሉ ከፊታችን እንዳለም አስታውቀዋል።
ብልህ ይመጥቅበታል ሞኝ ይወድቅበታል እኛ ግን ከብልሆዎች ወገን ልንሆን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የ2012 ዓመተ ምህረት ”ወደ ልዕልና እንመጥቃለን ገና‘ ያልነውም ለዚህ ነው ብለዋል።
ባገኘናቸው ድሎች ረክተን አንቀርም ባሳለፍናቸው ድሎች ታስረን አንቆምም ወደ ልዕልና እንመጥቃለን ገና ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ።
“መምጠቅ ወደ ከፍታ መዝለቅ ነው፤ ልክ እንደ መንኩራኩር፣ ልዕልና ከከፍታ ይለያል ክብር አለው፤ በቀላሉ ከሚደረስበት መዳረሻ ወደላይ እጅግ መላቅን ይፈልጋል፤ እንመጥቃለን ገና ወደ ልዕልና ስንል መታፈርና መከበር ወዳለው ከፍታ እንደ ምድር ስበት የሚስቡን ችግሮቻችንን አልፈን ለዚህ በተዘጋጁ እና በቆረጡ መጣቂዎች እና ባዘጋጀነው የ10 ዓመት ፍኖተ ብልፅግና መንኩራኩርነት ህብረ ብሄራዊነት በተሰኘ ማምጠቂያ ስፍራ ብልፅግና ወደተባለ ደርሰንበት ወደ ማናውቀው የመንፈስ፣ የቁስ እና የኢኮኖሚ ከፍታ እንመጥቃለን ማለታችን ነው” ብለዋል።
2012 በደስታና ሀዘን፣ በክብርና ውርደት፣ በኩራትና ሀፍረት የተሞላ ዓመት ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ ፈታኞች አሉን ያሉትን ድንጋዮች ሁሉ መወርወራቸውን ተናግረዋል።
“ሆኖም የኢትዮጵያ ጀግኖች የቻሉትን ሁሉ ለሀገራቸው ሰውተዋል፤ ትርፍ ነብስ ያላቸው እስከሚመስል ድረስ በመሆኑም በጀግኖቿ ብርታት መከራውን ሁሉ አልፋ ኢትዮጵያችን ዛሬም አለች” ብለዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዓይነት ነን እስከምንል ድረስ በወገኖቻችን ላይ መከራዎች መውረዳችውን፣ ልብን የሚከፍሉ በርካታ ወሬዎች መሰማታቸውን በማንሳት ነገር ግን ኢትዮጵያ ጨለማ የማይበግራት የብርሃን ሀገር፣ የብርቱ ህዝብ የፅኑ ዜጋ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ድቅድቅ የሚመስሉ ጨለማ የሚገፉ አስደናቂ ታሪኮችንም በዚሁ ዓመት ሀገሪቱ ማየቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አንስተዋል።
ለዓመታት የታገለችለት የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እና የመጀመሪያ ሳታላይት ማምጠቋን ያለፈው ዓመት ከፍታዎች ብለው ዘርዝረዋቸዋል።
“ወደ ብልፅግና ማማ ሊያወጣ ራእይ የሰነቀው፣ ከፋፋይ እና ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን በፍቅር እና በመተባበር የተካው፣ ሀገሪቱን ወደሚገባት ከፍታ ሊያወጣት የሰነቀው” ያሉት ፓርቲያቸው ጥይት እንኳን ኮሽ ሳይል የነበረውን አሮጌ አስተሳሰብ አስወግዶ የተወለደው በዚህ ዓመት ነበር ብለዋል።
ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ አስቀድማ ተዘጋጅታ መመከት የቻለችው፣ አረንጓዴ ሀገር ለመፍጠር 5 ቢሊየን ችግኝ መትከል የተቻለው፣ ነባር ባርኮቸን አልምቶ ለመጠቀም ምሳሌ የሆኑት የአንድነት ፓርክና እና የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የተጠናቀቁት፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች የዘመቱት፣ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም አርሻ ውጤታማ የሆኑት እና ለዓመታት ሲያሽቆለቁል የነበረው የወጪ ንግድ ወደ አድገት የመጣው በ2012 መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል።
“ከጨለማ በኋላ ብርሃን፣ ከፈተና በኋላ ተስፋ፣ ከመለያየት በኋላ መገናኘት፣ ከውድቀት በኋላ መነሳት አለ ከዘመን ወደ ዘመን የምናደርገው ሽግግር ትርጉም እንዲኖረው ካለፈው ዘመን ጋር አሮጌና ጎታች አስተሳሰባችንን ተሰናብተን አዲስ እና ተራማጅ አስተሳሰብን ልንላበስ ይግባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የቀጣይ ዓመት ውጤታችን የሚወሰነው ለመለወጥ በተዘጋጀነው መጠን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዐቢይ፥ የፖለቲካ አሰራራችንን እና ባህላችንን በቅንነት ለማሻሻል፣ በመካከላችን የፈጠርነውን የልዩነት አጥር ለማፍረስ፣ የመለያየትን ገደል ለመሻገር ምን ያህል ተዘጋጅተናል የሚሉ ጥያቄዎችን በመሰንዘር በዚህ አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ለእነዚህ ጥያዎች ሁሉም ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
“መጪው ዓመት ስላለፈው የምንቆዝምበት፣ ስላለፈው ቂም ቋጥረን በቀልን የምናስብበት ሳይሆን በይቅርታ እና በእርቅ ሰላምን አውርደን በመተሳሰብና በመደማመጥ ልዩነታችንን አጥብበን ህዝባችንን እና ሀገራችንን በማስቀደም ወደ ልዕልና የምንመጥቅበት እንዲሆን ሀላችሁንም እጋብዛለሁ” ብለዋል።
“የጀመርነውን የምንፈፅምበት፣ ያሰብነውን ወደ መሬት የምናወርድበት፣ ከዳር እስከዳር ስጋትና ግጭት ጠፍቶ በሰላም እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ሰርተን በጋራ የምንደሰትበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል ።