የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ዓመቱ መንግስትና ህዝብ በአንድነትና በአዲስ ስሜት እንዲሁም በትልቅ ተነሳሽነት ትልልቅ ስራዎች ያከናወኑበት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ቀጣዩ ዓመትም ለብልጽግና ጠንካራ መሰረት ለመጣል እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የምንሰራበት ነው ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በዚህ ዓመት የታቀዱ ስራዎችን ማሳካት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በሁሉም አቅጣጫ ፈተና ቢበዛም በአሸናፊነት ስሜት ተወጥተነዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ዓመቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበት እንደነበርም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ዓመቱ ቆራጥነትና መስዋዕትነት የጠየቀ ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ለውጥን ለማምጣት የተከፈለው መስዋዕትነት በቀጣዩ ትውልድ ውስጥ የራሱን ደማቅ አሻራ ያሳረፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በታቀደው መሰረት ቀንና ሰዓት ሳይዛነፍ መከናወኑ የህዝቡ አንድነትና አብሮነት ምስጢር መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡
በህዳሴ ግድብ የተገኘው ድል ከአድዋ በኋላ በታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ትልቅ ድል መሆኑንም ነው በመልዕክታቸው የገለጹት፡፡