የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ውጤትን በእጅ ስልክ በጽሁፍ መልዕክት ለማሳወቅ የሚያስችል አሰራር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ለተመርማሪዎች በ8335 በእጅ ስልካቸው የጽሁፍ መልዕክት እንዲደርሳቸው የሚያስችል ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የዲጂታላዜሺን የስራ ክፍል የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት በተቀላጠፈ መንገድ ለተመርማሪዎች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ኤሌክትሮኒካል በማድረግ የቫይረሱን የላቦራቶሪ ውጤት በእጅ ስልካቸው እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን ገለጸ።
የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የዲጂታላዜሺን የስራ ክፍል ሃላፊ አቶ መስዑድ ሙሐመድ፥ የላቦራቶሪ መረጃ ስርዓቱን ከማሳደግ አንጻር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን በተለይም በወረቀት ይደረግ የነበሩትን አብዛኞቹን መረጃዎች በኤሌክትሮኒክስ መለዋወጥ መጀመሩን ገልፀዋል።
ከዚህም ውስጥ የተለያዩ ስራዎች ክትትል የሚደርግባቸውን መንገድ፣ መረጃዎች የሚሰራጩባቸውን ዘዴ በየቀኑና በየሳምንቱ የሚላኩ ሪፖርቶች በወረቀት የነበሩት ቀርተው በኤሌክትሮኒክስ በማድረግ ስራዎችን የተቀላጠፉና በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የላቡራቶሪ ናሙና የተወሰደላቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ የናሙና ምርመራ ውጤት ከተረጋገጠ በኋላ ከሶስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በ8335 በጠቀም ተመርማሪዎች ውጤቱን በአጭር የጽሁፍ መልዕክት (SMS) እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል።
ውጤቱም በትክክል መድረሱን የሚያረጋግጥ የአሰራር ዘዴ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር እየተሰራ ሲሆን፥ ነገር ግን ተመርማሪዎች ትክክለኛ የስልክ ቁጥራቸውን ማስመዘገብ እንዳለባቸው አቶ መስዑድ ሙሐመድ አያይዘው ገልጸዋል።
ከላቦራቶሪ በተጨማሪ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በተቋማቸው በሚመረመሩ ታካሚዎች ላይ የሚያዩትን የኮሮና ምልክት በ8335 ወይም በሞባይል መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) በመጠቀም በጽሁፍ መረጃ ለኢንስቲትዩቱ የሚልኩበትን ሂደትና እራስን ለይቶ ህክምና እና እንክብካቤ እንዲሁም የተለየዩ የኮሮና ሎጂስቲክስ ልውውጥን አስመልክቶ ኤሌክትሮኒክስ በማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።