ጠ/ሚ ዐቢይ በሱዳን ቆይታቸው የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ስራ አከናውነዋል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን በነበራቸው የስራ ጉብኝት ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች የሁለትዮሸ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን የነበራቸውን የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
በነበራቸው ቆይታም ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና ከሽግግር መንግስቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም በዋናነት የህዳሴ ግድብን በተመለከተና በሌሎች ሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጉብኝቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ሽግግር ላይ መሆናቸው ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያና ሱዳን ወዳጅነት ከመሪዎች ባሻገር ህዝባዊ መሰረት እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱዳን ቆይታቸው የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነትን ይበልጥ ማስተሳሳር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ከሱዳን መሪዎች ጋር መምከራቸውንም ገልጸዋል።
ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ መጠነኛ ቅሬታ ስታነሳ መቆየቷን አስታውሰው፤ “መሪዎቹ ግድቡን በሚመለከት የሚነሱ ቅሬታዎችን በውይይት ብቻ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግድቡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሱዳንም ጥቅም እንዳለው ማስረዳታቸውን አቶ ገዱ አውስተዋል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መከናወኑ ደግሞ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ማበጀት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን መሪዎቹ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም አፍሪካ መር የሆነው ድርድር በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁለቱም ሃገራት መሪዎች በቁርጠኝነት ለመስራት መተማማን ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሜሪካ “ሽብርተኝነትን ትረጃለሽ” በሚል ሱዳንን ካስቀመጠችበት ‘ጥቁር መዝገብ’ እንድታነሳ በብርቱ መስራታቸውንም አንስተዋል።
”ሱዳን በዚህ መዝገብ ውስጥ መቀመጧ ደግሞ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል” ነው ያሉት።
በመሆኑም መሪዎቹ በውይይታቸው ኢትዮጵያንም ሆነ ሱዳንን የሚገጥማቸው ችግር የጋራ ጉዳት ማምጣቱ አይቀሬ መሆኑን በመግለጽ በማናቸውም ሁኔታ ተደጋግፈው ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የተናገሩት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም መሪዎቹ የትኛውንም አይነት ችግር በውይይት መፍታት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን አስረድተዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሱዳን ፖለቲካዊ ሽግግር በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውንም ሃላፊዋ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ከሱዳን ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ማንሳታቸውንም ነው የገለጹት።
መሪዎቹ የሁለቱ ሃገራት ስኬት ከቀጠናው ባለፈ ለአፍሪካ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በማመን ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት ለመስራት መተማመናቸውንም ሃላፊዋ ጠቁመዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በቅርቡ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ የተገለጸ ሲሆን፤ በቆይታቸውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።