ከአሰራር ውጪ የ16 ሰራተኞች ቅጥር እንዲፈጸም ያደረገው በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በጥቅም በመመሳጠር ከአሰራር ውጪ የ16 ሰራተኞች ቅጥር እንዲፈጸም ያደረገው ተከሳሽ በ14 ዓመት እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ።
የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ፈይሳ ዱደማ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ ተደራራቢ ክስ አቅርቦበት ነበር።
በዚህም ተከሳሹ ፈይሳ ዱደማ በ2015 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ለሚመደቡ ሰራተኞች በወጣ የቅጥር ማስታወቂያ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰራተኞች እያሉ ተከሳሹ ከሌሎች ሶስት ግብረዓበሮቹ ጋር በጥቅም በመመሳጠርና ስልጣኑን ያለአግባብ በመጠቀም የማይመለከታቸውን ማለትም መስፈርቱን የማያሟሉ 16 ግለሰቦች የስራ ቅጥር እንዲፈጸምላቸው እና እንዲመደቡ በማድረግ ያልተገባ 732 ሺህ 823 ብር የደመወዝ ክፍያ እንዲፈጽምና በተመሳሳይ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉ ተጠቅሶ ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበት ነበር።
ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ ክሱ ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ ክዶ በመከራከሩ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦበታል።
ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ጠቅሶ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።
በዚህም ተከሳሹ ተከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ተከሳሹን በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በተጨማሪም ተከሳሹ ቀደም ሲል በተፈቀደለት የ25 ሺህ ብር የዋስትና መብት መነሻ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቅረቱ ምክንያት ተጨማሪ የ280 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
ፍርድ ቤቱ የኦሮሚያ ፖሊስ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አውሎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብና የተወሰነበትን የእስራት ውሳኔ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እያለ የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ከዞኑ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ኃብት ቢሮ ጋር በመሆን በህገ-ወጥ መንገድ የስራ ቅጥር የተፈጸመላቸው 16 ሰራተኞች ከስራ እንዲታገዱ በማድረግ የተከሳሹ ግብረ አበሮች ናቸው በተባሉ ሶስት ግለሰቦች ላይ በፍርድ ቤቱ ክስ ማቅረብ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል።
በታሪክ አዱኛ