የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሁሉም በአቅሙ አክሲዮን በመግዛት ሃብት የሚያፈራበት ይሆናል – ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሁሉም በአቅሙ አክሲዮን በመግዛት ሃብት የሚያፈራበት ይሆናል ሲሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) አመለከቱ።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተከፈተው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በአብዛኛው አክሲዮን፣ የመንግስት ቦንድ፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ የኩባንያዎች ቦንድ እና ሌሎች ቦንዶች ወደ ማዕከላዊ ቦታ መጥተው የሚገበያዩበት መድረክ ነው፡፡
ገበያው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ የሚደረግበት ሲሆን÷ ለምጣኔ ኃብት እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የመንግስትን የፋይናንስ እጥረት ለመቅርፍ፣ የግሉን ዘርፍ በተለይ ሥራ ፈጣሪዎችን የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት እና ሥራ አጥነትን ይቀንሳል ብለዋል።
እንዲሁም ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ክፍተቶች ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ እድል ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረው፤ ተቋሙ ሁሉም ሰው በአቅሙ አክሲዮን በመግዛት ሃብት የሚያፈራበት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትና ስታርትአፖችም ወደ ገበያው መጥተው ታዳጊ ገበያ ላይ በመመዝገብ ካፒታላቸውን ማሻሻል የሚችሉበት መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ስርዓትን መገንባት የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያው አካል ነው ያሉት ጥላሁን ዶ/ር፤ በኢኮኖሚው የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ ማነቆ ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ እጥረት ለመፍታት ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በባንኮች ያሉ የብድርና የሌሎች አገልግሎቶች ገደቦችን እንደሚያስቀር አመልክተው፤ የፋይናንስ እድሎችን እንደሚሰጥና ከሸሪያ ህግ ጋር የተጣጣሙ ከወለድ ነጻ የሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲያስተዋውቅ ገልጸዋል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መጀመር ለመንግስት እና ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው