በማይናማር በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት ጥረቱን ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ማይናማር፣ታይላንድ ድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ወደሚገኙ ህገ ወጥ ካምፓች ተወስደው የሚገኙ ዜጎችን ለማስመለስ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷መንግስት ባደረገው ጥረት በስድስት ወራት ውስጥ 34 ዜጎች ከአጋቾች ነፃ ወጥተው ወደ ታይላንድ እና ወደ ኀገር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
ዜጎችን የመታደጉ ስራ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ቶኪዮ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሚስዮን በተጨማሪ በኒውዴልሂ የሚገኘው ኤምባሲም ተልዕኮ ተሰጥቶት መንቀሳቀስ መጀመሩን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ የመረጃ ማሰባሰብ እና ማጣራት ስራ በችግር ውስጥ እንደሚገኙ የታረጋገጡ የ380 ዜጎች ስም እና ፓስፖርት ቁጥር ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተለው ቶኪዮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚስዮን መላኩን ቃል አቀባዩ ጨምረው አስታውቀዋል።
ችግሩ ዓለም አቀፍ የወንጀል ገፅታ እንዳለው በመግለጽም÷ኢትዮጵያን ጨምሮ የ19 ሀገራት ዜጎች በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ማይናማር በመግባት ለከፋ ችግር ተዳርገው እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
ከስራ ቅጥር ጋር ተያያዥ በሆኑ የማታለያ ስልቶች ተወስደው የሚገኙባቸው አካባቢዎች ከሀገሪቱ መንግስት ቁጥጥር ውጭ መሆናቸው የማስመለሱን ስራ እንዳከበደው መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስት በተናጠል ከሚያደርጋቸው ጥረቶች በተጨማሪ ከማይናማር መንግስት እና ከሌሎች ችግሩ ከገጠማቸው ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡