ለ3 ሺህ ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እስካሁን ለ3 ሺህ ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ መደረጉን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
የውይይቱ አላማም ባንኩ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል በሚከፍተው አዲስ የዓይን ባንክ ቅድመ ዝግጅት የሚውል ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያን ደምና ሕብረህዋስ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በዚህ ወቅት÷ አዲስ የሚከፈተው የዓይን ባንክ በኢትዮጵያ ሁለተኛው የዓይን ባንክ መሆኑን ገልጸው ከ 6 ወራት በኃላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ለዓይነ ስውርነት እንደተዳረጉ እና እስካሁን 3 ሺህ ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንደተደረገላቸውም ጠቁመዋል።
በመድረኩ በጎ ፈቃደኛ የዓይን ብሌን ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የግንዛቤ ስራ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል።
በወርቃፈራው ያለው እና ሰሚራ ማሐመድያሲን