በጎንደር የጥምቀት በዓል ታዳሚዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋሲለደስ ቤተመንግስትን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መስሕብ እና የቅርስ ሀብት ባላት ጎንደር ከተማ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከሀገር ውስጥና ከውጪ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር የሚመጡ ታዳሚዎችን ለመቀበል ሁለንተናዊ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም የሚመጡ እንግዶች እነዚህን መስሕቦች እንዲጎበኙ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት ተቀዳሚ ከንቲባው፡፡
የከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለበዓሉ ታዳሚዎች ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
የጎንደር ሆቴሎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የጎሃ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አጥናፉ በበኩላቸው፥ ጥምቀትን በጎንደር ለሚያከብሩ የሀገርና የውጭ እንግዶች ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጎንደርን እንግዳ ተቀባይነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ለእንግዶች የአካባቢውን ባህልና ትውፊት የጠበቀ መስተንግዶ እንደሚሰጥም አንስተዋል።
ፋና ዲጂታል ያነጋገራቸው በጎንደር የሚገኙ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጆችም፥ ለጥምቀት በዓል ዝግጅት አጠናቅቀው እንግዶችን መቀበል መጀመራቸውን ተናግረዋል።
እንግዶች በቆይታቸው ከበዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ባለፈ ባህላዊ ውዝዋዜ፣ ምግብ አሰራር፣ ቡና አፈላልና ሌሎች ክዋኔዎችን እንዲገነዘቡ እንደሚያደረግም ጠቅሰዋል።
የጎንደር ከተማ ፖሊስ በበኩሉ÷ የጥምቀት በዓል በጎንደር በድምቀት እንዲከበር ከሚመለከታቸው አከላት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቋል፡፡
በመላኩ ገድፍ