የነዳጅና ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲቀጥል መንግስት ከፍተኛ ድጎማ አድርጓል – አቶ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነዳጅን ጨምሮ ስትራቴጂክ የሚባሉ ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ድጎማ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት መንግስት ባለፉት ዓመታት ከ267 ቢሊየን ብር ለነዳጅ ድጎማ ያደረገ ሲሆን÷ለ2017 ዓመት ብቻ ደግሞ ለነዳጅ ድጎማ ተጨማሪ 100 ቢሊየን ብር በጀት ጸድቋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተጠናክሮ ለኢኮኖሚው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሰፊ ሥራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ማሻሻያው የውጪ ምንዛሪ ግኝቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻ፣ ከልማት አጋሮች ጋር ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም እንዲሻሻል ጨምሮ የባንኮች የቁጠባ መጠን እንዲያድግ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
የምንዛሬ ተመኑ በገበያ እንዲወሰን ከመደረጉም ሊመጡ የሚችሉ የዋጋ ጭማሪዎች ህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድሩም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ነዳጅን ጨምሮ ስትራቴጂክ የሚባሉ ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ድጎማን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለደመወዝ ጭማሪ፣ ለመድኃኒት፣ ለመሠረታዊ ሸቀጦች፣ ለከተማና እና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ጨምሮ ለሌሎችም በዓመት ከ400 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በሕብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያስከትልም ሪፎርሙ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ሃላፊነት እየተሰራ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
መንግስት በሀገሪቷ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር በዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በመመደብ ነዳጅን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በውጪ ምንዛሪ የሚገዛውን የነዳጅ ምርትም በሀገር ውስጥ በብር እንዲሸጥ ከማድረግ በተጨማሪ በከፍተኛ የመንግስት ድጎማ ወደ ህብረተሰቡ እንዲተላላፍ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዓለም ዋጋ የሚገዛውን የነዳጅ ምርት ከዓለም ዋጋ በታች እንዲሁም ከጎሮቤት ሀገራትም ዋጋ በታች በከፍተኛ ድጎማ እያቀረበ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከውጪ የሚገባውን እንዲሁም በከፍተኛ ድጎማ ለህዝብ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በኮትሮባንድ ወደ ጎሮቤት አገራት እንዳይወጣ ግብረ ሃይል ተቋቆሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።