Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ስራ እደግፋለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የአውሮፓ ህብረት ትምህርት ሚኒስቴር ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየስራቸው ላሉ ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከሆኑት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት ሚኒስቴሩ ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በአጠቃላይና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፎች እየተተገበሩ ያሉ የለውጥ እርምጃዎችንና የትኩረት አቅጣጫዎችን አብራርተዋል።

በተለይም ጥራት ያለው ፍትሃዊ ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የቅድመ ልጅነት ትምህርት፣ የመምህራንን የማስተማር አቅም ማሳደግ፣ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ-ልማት ማሻሻልና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

አክለውም ፥ በትምህርት ዘርፉ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር አካላት የቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸውና የተማሪዎችን እኩል የመማር መብት የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት በጋራ መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገርን በበኩላቸው ፥ ትምህርት ሚኒስቴር ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራቸው ላሉ ስራዎች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሁለቱ አካላት በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው በሚቀጥሉበት ጉዳይ ላይም መምከራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.