ትራምፕ ነጩ ቤተ-መንግስት እንደገባሁ ከፑቲን ጋር እመክራለሁ አሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን እንደተረከቡ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ለሁለተኛ ጊዜ በትረ-ስልጣን የሚጨብጡት አነጋጋሪው ትራምፕ ከሥድስት ቀናት በኋላ ቃለ-መሃላ በመፈጸም ወደስልጣን ይመጣሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ስላለው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በኒውስማክስ ጥያቄ የቀረበላቸው ትራምፕ፥ መፍትሄው ፑቲን ነው ብለዋል፡፡
ፑቲን ከእኔ ጋር መወያየት ይፈልጋሉ፤ እናም እንወያያለን በማለት ገልጸዋል።
ይህ ውይይቱ አሁን ቢሆን ምኞታቸው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከውይይቱ በፊት ግን ወደነጩ ቤተ-መንግስት መግባት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ለዩክሬን የሚሰጠውን በቢሊየን ዶላር የሚቆጠረውን የአሜሪካ ድጋፍ አቋርጣለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ብዙ የስልክ ጥሪዎችን በማድረግም ጦርነቱን በ24 ሰዓት ውስጥ ማስቆም እችላለሁ ማለታቸውን የዘገበው አርቲ ነው፡፡
ሆኖም ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ትራምፕ እና የሽግግር ቡድን አባላቱ፥ የሀገራቱ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ወራት መቁጠር ግድ ሊሆን እንደሚችልም አምነዋል፡፡
በቃለ ምልልሳቸው ወቅት፥ በሁለቱ ሀገራት አስከፊ መዘዝ አስከትሏል ያሉት ጦርነቱ እንዲባባስ አድርገዋል ሲሉ ከነጩ ቤተ-መንግስት ሊሰናበቱ ቀናት የቀራቸውን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
የዚህ ችግር ምክንያት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ማነስ ነው ብለዋል።
ሆኖም ባይደን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ አስተዳደራቸው የወሰዳቸው እርምጃዎችን በስኬት ያነሳሉ፡፡