በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ የተገኘውን ሰላም ለማፅናት የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር እንዳለበት ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተገኘውን ሰላም ለማፅናት የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥመውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ውይይት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ተወካዮች፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ክልሎች መንግስታትና ባለድርሻ አካላት የጋራ ዕቅድ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመልክቷል።
በዚሁ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አጋጥሞ የነበረውን የጸጥታ ችግር በፌዴራል መንግስትና ክልሎች መንግስታት ርብርብ በሰላም ተፈትቷል፡፡
በባለድርሻ አካላት ቅንጅት የተከናወኑ ተግባራትም አካባቢው ወደ ቀድሞው ሰላም እንዲመለስ አስችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዛሬው መድረክ ዓላማም የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና ለማፅናት የግጭቶቹን መንስኤ መለየትና መፍትሄ ማስቀመጥ ነው ብለዋል።
በተለይ አሁን በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ለማፅናት መንግስትና ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና በመለየት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፥ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ማፅናት አለብን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ የቆዩና ዛሬ ላይ የደረሱ እንዲሁም ከተለያዩ ፍላጎቶች የመነጩ ችግሮች ለግጭቶች መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የግጭቶቹን መንስኤ በዘላቂነት ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፥ አሁንም በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡