በአማራ ክልል ከሩዝ ሰብል ልማት 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በ2016/17 ምርት ዘመን በመኸር ወቅት ከለማው የሩዝ ሰብል እስካሁን 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ እንዬ አሰፋ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ የሩዝ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ለሩዝ ሰብል ልማት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ከመለየት ጀምሮ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በመኸር ወቅት 270 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ለማልማት ታቅዶ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ያለው የሩዝ ዘር ብዜት አነስተኛ መሆን ሩዝን በስፋት ለማልማት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እስካሁንም 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት በኮምባይነር እና በሌሎች መንገዶች መሰብሰቡን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ የሩዝ ምርትን ለማሳደግ ከዘር ብዜት ጀምሮ ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ