የደም መርጋት …
አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፍቅርተ አዱኛ (ሥሟ ተቀይሯል) ትባላለች፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ስትሆን፥ የአንድ ልጅ እናት ከሆነች ደግሞ ገና 12 ቀኗ ነበር፡፡
በእርግዝና ወቅት ምንም ዓይነት የጤና እክል ያልነበራት ፍቅርተ፥ ልጇን በምጥ ከተገላገለች ጀምሮ እስከ 10 ቀን ድረስ ሠላማዊ የድህረ-ወሊድ ጊዜ አሳልፋለች፡፡
ይሁንና በእነዚህ ሁለት ቀናት እየተባባሰ የሚሄድ የግራ ታፋ ህመምና የመንቀሳቀስ ፈተናን መጋፈጥ ግድ ሆነባት፡፡ ባልጠና አራስ ጎኗ ሌላ ተጨማሪ ህመምና ስቃይ!
ከህመሟ እፎይታን እንድታገኝ አማራጭ ያለችውን መፍትሄ ብትጠቀም፤ ማስታገሻ መድኃኒት ብትወስድም ህመሙ ሊሻላት አልቻለም፡፡ እየባሰ እየጸናባት ሄደ፡፡
በዚህም የወሊድ አገልግሎት ወዳገኘችበት የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ታደርጋለች፤ በዚህም የደም መርጋት ችግር እንደገጠማትና በጤና ተቋሙ ተኝታ መታከም ነበረባት፡፡
ለሶስት ቀናት ያህል አስፈላጊው ህክምና ስታደርግ ከቆየች በኋላም ከጊዜ ወደጊዜም የጤና ሁኔታዋ እየተሻሻለ መጣ፤ ወደቤቷም ከህክምና ባለሙያዎች የተሰጣትን የጥንቃቄ ምክርና መድሃኒት ይዛ ተመልሳለች፡፡
ፍቅርተና ልጇ በጥሩ ጤንነት ላይ ቢገኙም ሌሎች እናቶች በግንዛቤ እጥረትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ለህልፈት የተዳረጉበት ችግር ነው የደም መርጋት፡፡
የደም መርጋት ችግር በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥሙ የከፍተኛ ህመምና ሞት ምክንያቶች አንዱ ሲሆን፥ ስለችግሩ በመገንዘብ መከላከል እንደሚገባ ይመከራል፡፡
የጽንስና ማህጸን ስፔሻሊስትና የእናቶችና የሽል ሠብ ስፔሻሊስት ዶክተር ያሬድ ተስፋዬ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የደም መርጋት ችግር በይበልጥ በእግር ላይ የሚከሰት ሲሆን፥ ከረጋው ደም ተላቆ የሚሄድ የረጋ ደም ቁራጭ ወደ ሳምባ የደም ዝውውር በመሄድ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል ያስረዳሉ፡፡
የችግሩ መጠን በኢትዮጵያ ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1000 ወላድ ውስጥ ሁለትና ከዚያም በላይ በሆኑ እናቶች ላይ እንደሚያጋጥም አንስተዋል፡፡
የደም መርጋት ችግር ከእርግዝና እና ከወሊድ በኋላ የሚበዛበት ምክንያት ተፈጥሯዊ በሆነ እርግዝና የሠውነት አሰራር ምክንያት ሲሆን፤ ይህም በእርግዝና ጊዜ በነፍሰጡር እናቶች ውስጥ ደም እንዲረጋ የሚያደርጉት ንጥረ-ነገሮች እና ሌሎች የሠውነት ቅመሞች (ሆርሞኖች) ከፍ በማለታቸው ነው ይላሉ፡፡
ከእርግዝና እና ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥመው የደም መርጋት ችግር የሚያሳያቸውን ምልክቶች በሁለት ይከፈላሉ።
የመጀመሪያው እግር ላይ የደም መርጋት ሲከሰት፡- የእግር ቆዳ መቅላትና የመሞቅ ስሜት፣ የእግር ህመምና እብጠት (በይበልጥ በግራ እግር)፣ በሚነካበት ጊዜ ህመም ሲሰማ እንዲሁም ለመራመድ መቸገር፤
ሁለተኛው ደግሞ የረጋ የደም ቁራጭ የሳምባ የደም ስርን ሲዘጋ፡- ለመተንፈስ መቸገር፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ የልብ ምት መጨመር፣ ከፍተኛ የድካም ስሜትና መዝለፍለፍ እንዲሁም ራስን መሳትን እንደሆኑ ባለሙያው አመላክተዋል።
እንደ ዶክተር ያሬድ ገለጻ፤ የረጋ የደም ቁራጭ የሳንባ የደም ሥርን ሲዘጋ እንደ ችግሩ ስፋትና መጠን ድንገተኛ ሞትን ሊያስከትል ስለሚችል ምልክቶቹ ከታዩ በአስቸኳይ ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል፡፡
የደም መርጋት ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ዋና ዋና ነገሮች ከዘር ሐረግ ጋር የተገናኘ የደም መርጋት ችግር፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ የደም ግፊት ችግር (በይበልጥ በእርግዝና የሚመጣና ከሽል መቀንጨር ጋር የተገናኘ)፣ በደም ልገሳ የተገኘ ደም በተደጋጋሚ (አብዝቶ) መውሰድ ናቸው።
በተጨማሪም የመንታ እርግዝና፣ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ ተያያዥ የውስጥ ደዌ ህመም፣ ከዚህ በፊት ያጋጠመ የደም መርጋት ችግር እና በተለይ ድንገተኛ የሆነ የቀዶ ህክምና ወሊድ የደም መርጋት ተጋላጭነትን ይጨምራል።
የደም መርጋት ችግርን ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም ነፍሰ ጡር ሴት የደም መርጋት ችግር እንዳያጋጥማት በተጋላጭነቷ መጠን በሀኪም በሚታዘዙ መድሃኒቶች መከላከል ይቻላል።
እንዲሁም ሁሉም በቀዶ ህክምና የወለዱ እናቶች ከወለዱ በኋላ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀውን ካልሲ እንዲጠቀሙ፣ በቂ የሆነ ፈሳሽ እንዲወስዱ፣ ቶሎ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በእርግዝና ወቅት በግራ ጎን መተኛት፣ ከእርግዝና በፊት የሠውነት ክብደትን ማመጣጠንና ተያያዥ የውስጥ ደዌ ህመም ካለ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ይመከራል።
ከዚህ በፊት የደም መርጋት ያጋጠማቸው ከማርገዛቸው በፊት ሀኪማቸውን ቢያማክሩ ሲሉም ዶክተር ያሬድ መክረዋል፡፡
በመሰረት አወቀ