በሎስ አንጀለስ በተከሰተ ሰደድ እሳት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በተከሰተ ሰደድ እሳት 30 ሺህ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መተላለፉ ተሰምቷል፡፡
ሰደድ እሳቱ በተከሰተ በሰዓታት ቆይታ ውስጥ ከ10 ሄክታር ወደ 2 ሺህ 900 ሄክታር መሬት መስፋፋቱ ተገልጿል፡፡
አደጋውን ተከትሎም በከተማዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን÷30 ሺህ ሰዎች አካባቢያውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መተላለፉም ተመላክቷል፡፡
በደቡብ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ የተከሰተው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ነፋስ የቀላቀለ በመሆኑ አሁን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ነው ተብሏል፡፡
በክስተቱ ቢያንስ 200 ሺህ ሰዎች የኤሌክትሪክ ሃይል የተቋረጠባቸው ሲሆን ፥ አንዳንድ ት/ቤቶች በከፍተኛ ነፋስና በሃይል መቆራረጥ ሳቢያ መዘጋታቸው ተጠቁሟል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ የሚውል በጀት ያጸደቁ ሲሆን ፥ በካሊፎርኒያ ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች አደጋ ላይ በመሆናቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡