የሸገር ከተማ የኮሪደር ልማት በሚጠበቀው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸገር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በሸገር ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዳሉት÷በአስተዳደሩ ከሶስት ወራት በፊት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በሚጠበቀው ልክ እየተከናወነ አይደለም፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራው በፍጥነት ባለመከናወኑም ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠናል ሲሉ ለፋና ዲጂታል ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ነዋሪዎች የኮሪደር ልማት ሥራን እንደሚደግፉ ገልጸው÷ሥራው በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወን ጠይቀዋል፡፡
የሸገር ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በተያዘው እቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመው÷አሁን ላይ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና ኢትዮ ቴሌኮም መስመር ዝርጋታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቅርቡም የኮሪደርል ልማት ሥራውን ሙሉ በሙሉ በመጀመር በፍጥነትና በጥራት ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በጸሃይ ጉሉማ