አቶ ኦርዲን የውሃ ብክነትን በመቀነስ አቅርቦትን ለማሻሻል እንደሚሰራ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል የውሃ ብክነትን መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት÷ በከተማም ሆነ በገጠር የክልሉ አካባቢዎች በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።
በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያጎለበቱና ውጤት እየተመዘገበባቸው እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በክልሉ የውሃ ምርት ማነስና ብክነት ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው÷ ችግሮቹን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የውሃ ብክነት መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ወደ ስራ መግባቱ በተለይም በከተማው የሚስተዋለውን ችግር በመፍታት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚባክነውን ውሃ በማዳንና ለተጠቃሚው እንዲደርስ በማድረግ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ጉዳት የደረሰባቸውን የውሃ መስመሮች ውሃው ሳይባክን በቀላሉ መጠገን የሚያስችልና የሚባክነውን ውሃ ቆጥቦ በከተማም ሆነ በገጠሩ አካባቢ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል።