Fana: At a Speed of Life!

በዕዳጋ ሐሙስና መቐለ በሚገኙ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ዕዳጋ ሐሙስና መቐለ በሚገኙ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ከ3 ሺህ 500 በላይ  የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል እያከናወነ ባለው  የመልሶ ማቋቋም አተገባበር፣ ያገጠሙ ተግዳሮቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በአክሱም ከተማ ምክክር አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የኮሚሽኑን እቅድ፣ የዲሞብላይዜሽን አተገባበር ሂደት ያቀረቡት ሌተናል ኮሌኔል ጎሳዬ ጥላሁን÷ ስከ ዛሬ ባለው ክንውን በዕዳጋ ሐሙስና መቐለ መለስ ካምፓስ ከ5 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ሰልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

ከሰልጣኞቹ ውስጥ 3 ሺህ 500 የሚሆኑት ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ማህበረሰቡ መላቀላቸውን የገለፁት ሌተናል ኮሎኔሉ÷ 1 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ በማዕከላት ውስጥ የተሃድሶ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በበኩላቸው ÷  የቀድሞ ተዋጊዎችን የዲሞብላይዜዝ የማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ  በቀጣይ በአድዋ ማዕከል እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡

ለዚህም ስኬት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ያሉት ምክትልኮሚሽነሩ÷ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የማዕከላዊ ትግራይ አርበኞች ኮሚሽን ምክትል ሃላፊ ኪሮስ ሃይለ በበኩላቸው÷ የተጀመረውን የመልሶ ማቋቋም  ትግበራ ከኮሚሽኑና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ገር በመቀናጀት በውጤት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በምክክሩ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የኮሚሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ከማዕከላዊ ትግራይ ዞን፣ ከዓድዋ እና ከአክሱም ከተማ እንዲሁም ከዓድዋ ወረዳ የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች  መሳተፋቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.