Fana: At a Speed of Life!

የመቻል ስፖርተኞች በስፖርቱ ዘርፍ የኢትዮጵያ አደራ አለባቸው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቻል ስፖርተኞች በስፖርቱ ዘርፍ ከተቋም ባለፈ የኢትዮጵያ አደራ አለባቸው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በናይጀሪያ አቡጃ በመላው አፍሪካ የጦር ሃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል ተካፋይ ለነበረው የመቻል አትሌቲክስ ቡድን አቀባበል አድርገዋል።

መቻል ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሞዴል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገራችንም በመዝገብ የተረጋገጠ ብዙ ታሪክ ያለው የአንጋፋ ስፖርተኞች መፍለቂያ ነው ብለዋል፡፡

መቻል በስፖርቱ ዘርፍ ከተቋም ባለፈ የኢትዮጵያ አደራ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ከአመታት በፊት ከደረጃ በታች የነበረውን አንጋፋውን መቻል የስፖርት ክለብ ዳግም እንዲያንሰራራ በርካታ ሥራዎች በትኩረት መሰራታቸውን ተናግረዋል።

የክለቡን የቦርድ አመራር በአዲስ አደረጃጀት ማዋቀር፣ በኢኮኖሚ ምክንያት ክፍተት እንዳይፈጠር ቀድሞ በጀት በመመደብ መቻልን ወደተፈለገው አቅጣጫ ማምጣት እየተቻለ መሆኑንም ገልፀው፤ በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ብቃቱ የተረጋገጠ በሁሉም ዲስፕሊን የተቀረፀ ስፖርተኞች ስለሚያስፈልጋት የመቻል ስፖርተኞች መበርታት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የመቻል ስፖርተኞች የኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ተምሳሌት መሆን አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

በናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው የመላው አፍሪካ የጦር ሃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል ሰባት ወርቅ፣ ስምንት ብር፣ ሁለት ነሐስ እና አስር ዲፕሎማ እንዳመጣ የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.