Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ አቀማመጥ ሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለወጪ ንግድ መር ኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረጉ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና ያለው የተፈጥሮ ሀብት ምርት አቀነባብረው ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኩባንያዎችን ተመራጭ ማድረጉ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ተፈጥሮ ሀብት፣ ሰላም እና ወጣት የሰው ኃይል ፓርኩ ባለሃብቶችን መሳብ እንዲችል ማድረጉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲ ተናግረዋል፡፡

በፓርኩ ሥራ ለመጀመር የፋብሪካ ተከላ እና የሼድ ግንባታ እያከናውኑ ያሉ ባለሀብቶች በክልሉ ያለውን የጨው ሀብት በማቀነባበር ለሰው እና ለእንሰሳት ምግብነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓት ያቀርባሉ ብለዋል፡፡

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማበረታታት የሰጠውን ትኩረትና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው የኢኮኖሚ ዞኖች ከፍተኛ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍላጎት መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው 10 በመቶ የሊዝ ቅድመ ክፍያ በተለየ ሁኔታ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ አምስት በመቶ ዝቅ መደረጉን እና ክፍያውም ከዶላር ወደ ብር መቀየሩን አስታውሰዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ 177 የማምረቻ ሼዶች መካከል ከ86 በመቶ የሚልቁት በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡

በሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሠረተ-ልማት የተሟላላቸው 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው የማምረቻ ሼዶች ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ሆነው ባለሀብት በመጠባበቅ ላይ እንደሆነም የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.