የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ባንኩ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ክልል ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ሊያንድሬ ባሶል (ዶ/ር) በመድረኩ÷ ባንኩ የአፍሪካን ልማት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም መንገድ መሰረተ ልማቶች፣ ኢነርጂ፣ ትራንስፖርት፣ ግብርና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎች በአህጉሪቱ እንዲከናወነ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶችም ድጋፍ በማድረግ ትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች፣ የጤና ተቋማትንና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ እዉን ማድረግም ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው÷ ባንኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።