በ9 ክልሎች እና በ2 ከተማ አሥተዳደሮች አጀንዳዎች ተሰብስበዋል – ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስከ አሁን በዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት ከተማ አሥተዳደሮች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳዎች በሕዝባዊ ውይይቶች መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኪሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
እስከ አሁን ባለው ሂደትም በዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት የከተማ አሥተዳደሮች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳዎችን በሕዝባዊ ውይይቶች መሰብሰቡን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ እንደሚሰበስብ አመላክቷል፡፡
በዚህ ሂደት ባለድርሻ አካላት ተብለው የተለዩት እና ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ውስጥ እያሳተፋቸው የሚገኙት አካላት በየወረዳው ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የመምህራን ማኅበር፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ክልላዊና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአሠሪዎች ማኅበራት እና የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን መሆናቸውን ጠቅሷል።
እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ የክልል መንግሥት (አስፈጻሚ አካላት)፣ የክልል ዳኞች፣ የክልል ምክር ቤት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሚዲያ ተቋማት (ጋዜጠኞች) ማኅበር፣ የቀድሞ ሠራዊት ማኅበራት፣ የንግድ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸውን አስታውሷል።