Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ2030 በኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል ላይ ያስቀመጠችው ግብ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ2027 በኤች አይቪ አዲስ የመያዝ እና የሞት ምጣኔን ወደ 1/10000 ሰዎች ዝቅ በማድረግ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭትን የመቆጣጠር እና በ2030 ደግሞ ዜሮ የማድረስ ግብ አስቀምጣለች።

የጥናት ውጤቶች እንደሚያመላክቱት በፈረንጆቹ 2023 በኢትዮጵያ 605 ሺህ 238 ወገኖች ቫይረሱ በደማቸው አለባቸው የሚል ግምት ነበር።

ከነዚህ ውስጥ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ያወቁ 547 ሺህ ያህሉ ወገኖች ሲሆኑ÷ ውጤታቸውን ካወቁት መካከልም 94 በመቶ ያህሉ የፀረ-ኤች አይቪ መድኃኒት እየወሰዱ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ የቫይረሱን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔ በ2027 ወደ 5 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔው ከ10 ዓመት በፊት 40 በመቶ እንደነበር እና ይህን አሃዝ አሁን ወደ 8 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ባለው ርብርብ በቫይረሱ አዲስ የመያዝ ምጣኔ በ2001 ዓ.ም ከነበረበት 133 ሺህ አሁን ላይ ወደ 7 ሺህ አካባቢ ዝቅ ማለቱንም አስረድቷል፡፡

እንዲሁም የሞት ምጣኔ ከ10 ሺህ ወደ 9 ሺህ ዝቅ ማለቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ÷ አሁንም በተለይ ወጣቶች ላይ በሚፈለገው ልክ እየቀነሰ ባለመሆኑ የተቀናጀ ጥረት ያሻል ነው ብሏል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት አሃዞች እንደሚያመላክቱት በቫይረሱ አዲስ የመያዝ፣ የሞት እና ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔ ከነበሩበት አንፃር እየቀነሱ ቢሆንም÷ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ አስገንዝቧል፡፡

ይህም በ2027 ሊደረስበት የተቀመጠውን በሁሉም ክልሎች በቫይረሱ አዲስ የመያዝ እና የመሞት ምጣኔን ወደ 0 ነጥብ 01 ዝቅ የማድረግ ግብ ለማሳካት ማኅበረሰቡን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ ይናገራሉ።

ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት እና የሐይማኖት ተቋማትን ጨምሮ አጋር አካላት እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበል።

አዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ ጋምቤላ ክልል፣ ድሬዳዋ አሥተዳደር፣ ሐረሪ ፣ ትግራይ እና አማራ ክልሎች በቅደም ተከተላቸው የቫይረሱ ሥርጭት ከፍ ያለባቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በከተሞች ያለው የቫይረሱ የሥርጭት መጠን በገጠሩ ካለው በ 7 እጥፍ እንደሚበልጥ ገልፀው፥ ለአብነትም ሥርጭቱ በከተሞች 2 ነጥብ 9 ሲሆን በገጠር 0 ነጥብ 4 መሆኑን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያም የኤች አይ ቪ ኤድስ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት ጀምሮ ባሉ አዋቂዎች መካከል ያለው የሥርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 87 በመቶ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

ይህ ማለትም ከ100 ሰዎች አንዱ ቫይረሱ በደሙ እንደሚገኝ ይገመታል ማለት ነው ይላሉ።

ቫይረሱን በመከላከልና መቆጣጠር ሂደትም ወረዳዎችን ባላቸው በኤች አይ ቪ አዲስ የመያዝ ምጣኔ መሰረት በቅደም ተከተል በማስቀመጥ በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ላይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ውጤት ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በ300 ወረዳዎች ከፍተኛ፣ በ400 ወረዳዎች መካከለኛ እና በቀሪዎቹ ዝቅተኛ የቫይረስ ሥርጭት መኖሩን ለይተናል ይላሉ።

ሥርጭቱን ለመከላከል ከሚተገበሩት አገልግሎቶች መካከል ኮንዶምን በበቂ ሁኔታ ማሰራጨት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በየዓመቱ 55 ሚሊየን ኮንዶም ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገባ አረጋግጠዋል።

ይህም በተለያዩ አካላትና በንግዱ ማኅበረሰብ የሚገባውን እንደማያካትት ነው ያስገነዘቡት።

ከኤች አይ ቪ መከላከላያ፣ መመርመሪያ ኪቶች እና የሚወሰዱ መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ አሁን የአቅርቦት እጥረት አለመኖሩንም ነው ያረጋገጡት፡፡

ምናልባት በተለያየ ምክንያት ተደራሽነቱ ላይ ክፍተት እንዳይኖር በየደረጃው በሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት በኩል ትኩረት መሰጠቱን አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.