Fana: At a Speed of Life!

ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የሚደግፍ ፕሮጀክትን ወደ ሥራ ለማስገባት ያለመ ምክክር ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የሚደግፍ ፕሮጀክት በፍጥነት ወደ ሥራ በሚገባበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ፡፡

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በአፍሪካ ልማት ባንክ የሰው ኃይል፣ ወጣቶችና ክኅሎት ልማት ዳይሬክተር እና የሥርዓተ-ፆታ፣ የሴቶችና የሲቪል ማኅበረሰብ መምሪያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ማርታ ፍሪ (ዶ/ር) ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በውይይታቸውም ከባንኩ ጋር በክኅሎት ልማትና በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የትብብር ሥራዎችን ለማጠናከር ብሎም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መምከራቸውን ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በግብርና ዘርፍ አተኩረው የሚሠሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታዎች በዝርዝር ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በክኅሎት ልማት መስኩ የሀገር በቀል ዕውቀትን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማሰናሰል ጥራት ያለው የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠሩ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ በዘርፉ እየሠራች ያለውን ሥራ ለሌሎችም ተሞክሮ እንደሚሆን በመግለጽ ተሞክሮውን ማስፋት ላይ በትብብር ለመሥራት ተስማምተናል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.