Fana: At a Speed of Life!

የእስያ መሠረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በኢነርጂ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን እንደሚደግፍ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ የምታከናውነውን ዘርፈ-ብዙ ተግባር እንደሚደግፍ የእስያ መሠረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ አስታወቀ፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) የባንኩ ፕሬዚዳንት እና የቦርዱ ሊቀ-መንበር ከሆኑት ጂን ሊኩን ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ተቋማቸው በመጠጥ ውኃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ዘርፍ፣ በውኃ ሀብት አሥተዳደር እና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገራት ድጋፍ እንፈልጋለን ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኃይል ማመንጫ መሠረተ-ልማቶች ላይ ስኬታማ ለመሆንና ቀሪውን የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ላይ ባንኩ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔ ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ ኃይል እያቀረበች መሆኗን አስታውቀው÷ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ስላለ ባንኩ እንዲደግፈን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ መሠረተ-ልማት ለመዘርጋት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) ናቸው፡፡

ጂን ሊኩን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀው÷ በምን ጉዳዮች ላይ መተባበር እንደሚያስፈልግ በመለየት፣ የጎረቤት የኃይል አቅርቦት ጥያቄ እና የአየር ንብረት ለውጥ መቀነስ ላይ በትብብር እንሠራለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.