Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና እስያ መሠረተ ልማት ባንክ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና እስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በባንኩ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

በዚሁ ወቅት ጌዲዮን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እየተገበረች ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፎች እየተሰሩ ስለሚገኙ ስራዎች ለባንኩ ገለፃ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በያዘችው የልማት ኘሮግራም የምትገነባቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት አውታር ኘሮጀክቶች ከሀገር ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ያላቸው ሚና ቁልፍ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ ግዙፍ የመሰረተልማት ኘሮጀክቶችን ባንኩ ፋይናንስ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ኘሬዚዳንት ጂን ሊኩን በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ አምቅ የእድገት አቅም ያላት እና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያላች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ባንኩ ቁልፍ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ዙሪያ ከመንግሥት ጋር በቀጣይ አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በፈረንጆቹ 2016 የተመሰረተ ሲሆን÷ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ ቁጥር 110 ደርሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.