Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የጀርመን ግንኙነትን ወደ ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማሸጋገር ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የጀርመን ግንኙነትን ወደ ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ወልፍጋንግ ዶልድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፥ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ላላት ግንኙነት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጥና ጀርመን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት በፋይናንስና በቴክኒክ የምታደርገው ድጋፍ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር የምታደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ወልፍጋንግ ዶልድ በበኩላቸው፥ የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰላም ማስከበር ዙሪያ የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት 120 ዓመታት የደፈነ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የፖለቲካ ምክክር በማድረግ ወደ ሁሉን አቀፍ ትብብር ማሸጋገር በሚቻልበት አግባብ ላይም መወያየታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.