Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው- አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት፣ በህይወት የመኖር ዋስትናችን ነው ይላሉ።

“የሰላም እጦት ቤተሰብንና ሀገርን ይጎዳል” ያሉት አርሶ አደሮቹ÷ የሚኖሩበት አካባቢ ሰላም በመሆኑ የግብርና ስራቸውን በአግባቡ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይነትም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሁሉ በንግግር የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ÷ በዞኑ የሰላም ማስከበርና የልማት ስራዎች ጎን ለጎን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም አብዛኛዎቹ ወረዳዎች ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለሳቸው መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው÷ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የተሻለ የሰላም ሁኔታ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ የፖለቲካ አመራሩና ህዝቡ ባደረጉት ርብርብ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የተሻለ ሰላም በመኖሩ የግብርና ልማትና ሌሎችም ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በጫካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም በሰላም እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፥ አንጻራዊ ሰላምን ወደ አስተማማኝ ሁኔታ ለማሸጋገር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

አመራሩ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በግንባር ቀደምነት መሰለፍ እንዳለበት የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ህዝቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍም የማስተባበር ሚናውን ይወጣል ብለዋል።

መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸው፥ በጫካ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎችም ፍላጎታቸውንና ሀሳቦቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ከመንግስት ጋር እንዲወያዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም ሁሉም ተባብሮ ክልሉንና ሀገርን ወደ ከፍታ የሚወስድ ስራ መስራት ላይ ማተኮር ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.