Fana: At a Speed of Life!

በኮንፍረንሱ ሪፎርሞች ያመጡትን ለውጥ ማሳየት ተችሏል-አቶ ብናልፍ አንዱዓለም

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተካሄደው አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ ሪፎርሞች ያመጡትን ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት የተቻለበት ስኬታማ መድረክ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

“የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ ትናንት ተጠናቋል፡፡

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎችም ከውይይቱ በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም÷ በጉባኤው ከ22 ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ተወካዮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የአፍሪካን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችል ሰፊ ውይይት የተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በድንበር አካባቢ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ እንዲሁም ህገ ወጥ እንቅስቃሴን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረትን አጀንዳ 2063 እውን በማድረግ የአፍሪካን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን ምን መሰራት እንዳለበትም ምክክር ተደርጓል ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ሰላምና ብልጽግና የወሰደችውን የተግባር ርምጃ ያቀረበችበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በጸጥታና ደህንነት ተቋማት በነበራቸው ጉብኝትም የኢትዮጵያ ሪፎርሞች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን በተግባር እንዲያዩ አስችሏልም ነው ያሉት፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የተካሄደው አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ ሪፎርሞች ያመጡትን ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት የተቻለበት ስኬታማ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ጉባኤው እንዲካሄድ ሁሉም ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ በአህጉራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የተለያዩ ሀገራት የመከላከያና ደህንነት ተቋማት ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ የገነባቻቸው የሰላምና ደህንነት ተቋማት ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.