3ኛ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት እና ከቻይናው ሻንጋይ ኢንጂነሪንግ ሴንተር የኢትዮጵያን 3ኛ ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
ETRSS-2 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሳተላይት በጋራ አልምቶ ለማምጠቅ ነው ስምምነቱ የተደረገው።
በመሆኑም ሶስተኛዋን ሳተላይት ለማምጠቅ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ዓለም አቀፍ ግልፅ የጨረታ ሂደትን በመከተል የተካሄደው የግዢ ስርዓት ተጠናቆ ከአሸናፊው ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ሰነድ ተፈርሟል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደገለጹት፤ በስምምነቱ የ18 ወራት የማልማት ስራ ይከናወናል።
ኢንስቲትዩቱ ዘንድሮ 12 ሜትር የመሬት ምልከታ ሳተላይት መረጃ መቀበያ ግራውንድ ስቴሽን ገንብቶ ወደ ስራ እየገባ መሆኑንም ተናግረዋል።
3ኛውን የመሬት ምልከታ ሳታላይት ለማምጠቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በመስኩ ያለውን የተማረ የሰው ሀይል ችግር ለመቅረፍም ከአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ስልጠና እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በስንታየሁ አበበ