የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በደራ ወረዳ የተፈፀመውን አሰቃቂ የግድያ ድርጊት አወገዘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተፈፀመውን አሰቃቂ እና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ድርጊት አወገዘ፡፡
የጉባኤው ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ሁሉም ሀይማኖቶች የሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን፣ መታዘዝን፣ ይቅርታንና ዕርቅን አስቀድመው እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ንፁሀን ላይ ያነጣጠሩ የግድያ እና የእገታ እንዲሁም ማፈናቀል ድርጊቶች እየተፈፀሙ ነው ብለዋል።
ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ የሀይማኖት አባቶችን እያሳሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጉባኤው ገለልተኛነቱን ጠብቆ ግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላትን ለማነጋገርና ለማስታረቅ ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል።
ግጭትና ጦርነት ውጤቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ ኪሳራ በማድረስ የሀገርን ውስን ሀብት የሚያጠፋ እና የትውልዱን ተስፋ የሚያቀጭጭ በመሆኑ ጦርነትንና ተያይዘው የሚመጡ የሰላም ጠንቆች በቃችሁ ሊባሉ እንደሚገባ ተገልጿል።
በበረከት ተካልኝ እና ቤዛዊት ተፈሪ