የሱዳን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድጋፍ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ ለመደገፍ ኢትዮጵያ ቁርጠኝነት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሱዳን አቻቸውን አምባሳደር አሊ የሱፍ አህመድ አል ሻሪፍን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሁለትዮሽ ጉዳዮችና በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሱዳን ስላለው ሁኔታ ባደረጉት ገለጻ፥ በግጭቱ የሚሸሹ የሱዳን ዜጎችን ለመቀበል ኢትዮጵያ ላደረገችው መልካም መስተንግዶ እና ድጋፍ በህዝቡ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሱዳን ዜጎችን ማስተናገድ የጉርብትና ግዴታችን ነው ሲሉ ምላሽ የሰጡት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን አጋርነት አረጋግጠዋል።
በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ ለመደገፍ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነትን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
አክለውም፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረጉ ድርድርን ጨምሮ ቀጥታ ውይይት እና የጋራ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ ጠቀሜታውን ማመልከታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጎልበት በየጊዜው የሁለትዮሽ ፖለቲካዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።