አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕጻናት መጠነ-መቀንጨርን ዜሮ በማድረግ ጤናማ እና አምራች የሰው ኃይል ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ፡፡
በክልሉ የተቋቋመው የሥርዓተ-ምግብ እና ኒውትሪሽን ምክር ቤት ማብሰሪያ እና የግንዛቤ ማስጨቀጫ ስልጠና ላይ አቶ ኦርዲን ባደረጉት ንግግር÷ አካላዊና የአዕምሮ ዕድገቱ የዳበረ ጤናማ ትውልድን መገንባት ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳን መርሐ-ግብር ከተጀመረ ወዲህም በክልሉ የመቀንጨር ችግር በአንፃራዊነት መቀነስ መቻሉን እና የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሥርዓተ-ምግብ ችግርን ከመቅረፍ ጀምሮ ትውልዱ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል መጠነ-መቀንጨርና መቀጨጭን ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና ምርታማነትን በማጎልበት የማኅበረሰቡን ሥርዓተ-ምግብ ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበው÷ የትምህርት ቤቶች ምገባም የሥርዓተ-ምግብ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲቻል መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡