አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊየኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ አይደለም – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት በአርአያነት የሚጠቀስ ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊየኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት ‘Do they know its Christmas?’ ሙዚቃ አሁን ላይ ዳግም መለቀቁ የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በ1977 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ሰፊ ጉዳት ተከትሎ አየርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍና መሰል እውቅ ሙዚቀኞች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ‘Do they know its Christmas?’ የሚል ሙዚቃ አቀንቅነው ከፍተኛ ድጋፍ አሰባስበዋል።
የዚህ የሙዚቃ 40ኛ ዓመት ዘንድሮ የተከበረ ሲሆን÷ በወቅቱ የተሰራው ሙዚቃ ዳግም ተለቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሙዚቃው 40ኛ ዓመት ሲዘከር ሙዚቃው ዳግም እንዲለቀቅ መደረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መናገራቸውን “ዘ ታይምስ” ጋዜጣን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙዚቃው ላይ እንደተገለጸችው ሳትሆን በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል።
ሙዚቀኞቹ በወቅቱ የሰሩት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ሙዚቃው ዛሬ ላይ ከጊዜው ጋር አብሮ አለመሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ሙዚቃው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎቿ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ያለች ሀገር ሆና ብትታወቅ ይጠቅም ነበር ብለዋል።
ሙዚቃው አሁን እኛ ለምንፈልገው ኢንቨስትመንት የሚጠቅም አይደለም፤ ድርቅ አሁን ላይ እኛን እንደ አህጉርም ሆነ እንደ ሀገር አይገልጸንም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንፆት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እና በሌሎች መስኮች እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ዳግም ረሃብ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውንም ጠቅሰል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ችላለች፤ ሌሎች ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት አቅም ፈጥራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና ዘርፍ አብዮት እያካሄደች መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ይህ ሙዚቃ የተለያዩ ወቀሳዎች እየደረሰበት መሆኑንም “ዘ ታይምስ” ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።
ሙዚቃው በፈረንጆቹ 2014 እንደ አዲስ ሲሰራ እውቁ እንግሊዛዊ ኢድ ሺራን በሙዚቃው ከተሳተፉ አርቲስቶች መካከል አንዱ ነበር።
ይሁንና አሁን ላይ ሙዚቃው የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንደማይገልጽ በሚሰነዘርበት ወቀሳ በወቅቱ በሙዚቃው ተሳትፎ ባላደረኩ እስከማለት መደርሱም በዘገባው ተጠቅሷል።
በመድረክ ስሙ ፉስ ኦ ዲ ጂ የተሰኘው የጋና ሙዚቀኛ፤ ሙዚቃው የተጠቀማቸው የግጥም ስንኞች አፍሪካን በተመለከተ አሉታዊ መልዕክት እንዳላቸው ገልጿል።
ይህም የአፍሪካን ልማት፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እድገት ያቀጭጨዋል ነው ያለው።
ይህንን መልዕክቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራ ሲሆን እውቁ ሙዚቀኛ ኢድ ሺራንም ይህንን መልዕክት ተጋርቶታል።